የአጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በ2014/2015 የምርት ዘመን ከ1200 ሄክታር በላይ መሬት በሰብል በመሸፈን በአሁኑ ሰዓት ምርት በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡
ኮሌጁ የእርሻ ማሽነሪዎችን በውስጥ ገቢ በተወሰነ ደረጃ በማሟላት የሚያለማውን መሬት በሄክታር ከፍ በማድረግ ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለፋብሪካ ግባቶች እና የዘር ብዜት ሥራ ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁም መሠረት የገብስ ሰብሉን ለመሰብሰብ ኮሌጁ ያለው አጭዶ መውቂያ ማሽን 1/አንድ/ ብቻ በመሆኑ በተጨማሪ 2/ሁለት/ ማሽን በመከራየት በድምሩ በ3/ሶስት/ አጭዶ በሚወቃ ማሽን ምርቱን በመሰብሰብ ላይ ሲሆን በኩንታል ከሃያ ሺህ በላይ የገብስ ምርት ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡
ጎን ለጎንም ለእንስሳት መኖ የሚሆን የገለባ ማሰሪያ ማሽን በመከራየት ለኮሌጁ እንስሳት እርባታ ዘርፍ ለመኖ የሚሆን ገለባ የተሰበሰበ ከመሆኑም በላይ ለአከባቢው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የታሰረውን ገለባ በሽያጭ በማቅረብ ለአከባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ካሮት፣ቀይ ሥር፣ጥቅል ጎመንና ድንች በማምረት ለኮሌጁና ለአከባቢው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በሽያጭ እያቀረበ ሲሆን በ5/አምስት/ ሄ/ር መሬት ላይ የለማው የበርበሬ ምርት በመሰብሰብ ላይ ሲሆን በኩንታል እስከ አንድ መቶ ኩ/ል ምርት ይጠበቃል፡፡
እየተሰበሰበ ያለው የበርበሬ ምርት በቀን ስራ የሚሰሩ ሠራተኞች እጥረት በመከሰቱ የኮሌጁ ሠራተኞችና ተማሪዎች በርበሬውን ከብክነትና ጥፋት ለመከላከል ሲባል በፕሮግራም በመውጣት በ3/ሶስት/ ሄ/ር መሬት ላይ ያለውን የበርበሬ ምርት ሰብስበዋል፡፡ 
 

Leave a Comment