የአጋርፋ ግ/ቴ/ሙ/ት/ሥ ኮሌጅ ለባለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት፤ በአራት የትምህርት ዓይነቶች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ 305 ተማሪዎችን ለ 10ኛ ዙር፤ በደረጃ አራት የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ያስመረቀ ሲሆን ከነዚህም መካከል 91 ሴት ተመራቂዎች ናቸዉ፡፡
ኮሌጁ ሰልጣኞችን ያስመረቀው በአራት የትምህርት ዘርፎች ማለትም በእንሰሳት ሳይንስ፤ በእፅዋት ሳይንስ፤ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ እና በአነስተኛ መስኖ ልማት ሲሆን የእለቱን ተመራቂዎች ጨምሮ ከ1994 ዓ.ም ወዲህ ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ክብርት ወ/ሮ ነብሐ መሀመድ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት በእስካሁኑ የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ሂደት የተገኙትን ተጨባጭ ውጤቶችና ተሞክሮዎችን በመቀመር፣ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በማፍለቅና በማላመድ ወደ አምራቹ አርሶ አደርና አርብቶ አደር በብቃት ለማድረስና ወደ ተግባር ለማሸጋገር የተመራቂዎች ሚና ወሳኝ እንደሆነ በማስታወስ ይህን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሌት ተቀን ተግተው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
አጋርፋ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ የተቋቋመበት ዓላማ የሃገሪቱን ልማት፣ፖሊሲና ስትራቴጅ መሰረት በማድረግ በግብርናው ዘርፍ በመካከለኛ የሙያ ደረጃ በክህሎት እና በእውቀት ብቁ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት መሆኑን እና የእለቱ ተመራቂዎችም በቆይታቸው የቀሰሙትን የተግባርና የቲዎሪ እውቀት አጣምረው ወደ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አካባቢ በመመለስ ሙያቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡ እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ጫላ ፈየራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በዚሁ ዕለትም የኮሌጁ ሠራተኛና ነዋሪ ህፃናት ልጆች የሚማሩበት 5 ክፍል ያለው መዋዕለ ህፃናት አዲስ ህንፃ በውስጥ ገቢ ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ተገንብቶ የተጠናቀቀው መዋዕለ ህፃናትም በዕለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ወ/ሮ ነብሐ መሀመድ ተመርቋል፡፡